ምክረ ካህን



በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

“የሚመክር ቢሆን በመምከሩ ይትጋ” ሮሜ 12÷6-8



መንፈሳዊ የምምክር አገልግሎት ከእግዚአብሔር በተሰጠ ጸጋ የሚከናወን መሆኑን ቅዱስ ጳውሎስ  በሮሜ መልዕክቱ ምዕራፍ 12 ላይ ገልጾአል፡ በቅድስት ቤተክርስቲያን በዓውደ ምሕረት በስብከት እና በተለያዩ መርሐግብሮች ከምንሰጠው የሰውን ልጆች የመቅረጽ እና የዘለዓለማዊ መንገድን የማሳየት አገልግሎት በተጨማሪ መንፈሳዊ የምክክር አገልግሎት እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ ይ¤ውም በአሁኑ ወቅት ብዙ ሰዎች በማኀበራዊና ሥነ-ልቦናዊ ችግሮች የተጠመዱ ስለሆነ ነው፡፡

ለመሆኑ የመንፈሳዊ የምክክር አገልግሎት አስፈላጊነት ምንድነው?

       1.    ሥነ- ልቦናዊ እርዳታ ስለሆነ፡

ቅዱስ ጳውሎስ “ከእናንተ እያንዳንዱ የአንዱን ሸክም ይሸከም” ገላ 6፣1 ብሎ እንዳስተማረው የሰዎችን ሸክም ከምናቀልበት እርዳታ ዋነኛው ምክክር ነው ከአካላዊ ፣የኢኮኖሚያዊ፣ እገዛ የበለጠ የሥነ-ልቦና እገዛ ወሳኝ ነው፡፡ የሰው ልጅ ገንዘብና እውቀት ይዞ ደስታና መረጋጋት ከሌለው ምን ዋጋ አለው? ስለዚህም ከቀቢጸ ተስፋ እንዲወጡ ፣ በእግዚአብሔር እንዲታመኑ፣ ደስታ የተሞላበት ሕይወት እንዲመሩ ለማስቻል መንፈሳዊ የምክክር አገልግሎት አስፈላጊ ነው፡፡

               2.   በግልና በጥልቀት የሚደረግ ስለሆነ፡-

በርካታ አገልግሎቶቻችን በአደባባይ ሲሆኑ ምክክር ግን ተመካካሪና አመካካሪ (ካህን) ለብቻቸው ሆነው ጥልቅ ችግሮችን እና መፍትሔዎች ላይ ስለሚመካከሩ እጅግ ውጤታማ ነው፡፡ በአደባባይ አገልግሎት እያንዳንዱ ሰው ተምሮ ለለውጥ ቢዘጋጅም ነገር ግን ስለ ችሎታው፣ ችግሮቹ፣ መፍትሔዎቹ ወ.ዘ.ተ የመነጋገር አጋጣሚ የሚያገኘው እና በዓውደ ምሕረት የተማረውን በሕይወቱ የሚተገብረው በምክክር ሲታነጽ ብቻ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡

              3.    ምሥጢር የሚጠብቅ  ስለሆነ፡-

የዚህ አገልገሎት አማካሪው (ካህን) ለምክክር የመጣውን ሐሳብና ችግር በምሥጢር የመጠበቅ መንፈሳዊ ግዴታ አለበት፡፡ ይህም በመሆኑ ተመካካሪው ችግሩን ሳይፈራና ሳይጠራጠር መግለጽ የሚችልበት የምክክር አገለግሎትና መፍትሔ ማግኛ በመሆኑ ውጤታማ ነው፡፡ በአደባባይና ላላመኑበት ሰው ሊያወያዩት የማይችሉትን የውስጥ ችግር ሊቀርፍ የሚችል ተግባር ከመንፈሳዊ የምክክር አገልግሎት በይበልጥ በንስሐ አባትና ልጅ መካከል እንደሚፈጸመው አገልግሎት የተሻለ አይኖርም፡፡

በአጠቃላይ ምክክር እጅግ አስፈላጊ ሲሆን ነገር ግን ካህናትም ሆንን የተለያዩ የቤተክርስቲያን የአገልግሎት ክፍሎች ትኩረት ሰጥተነው ስንተገብር በብዛት አንታይም በግልጽ ቤተክርስቲያን የምክክር አገልግሎት ክፍሎች ትኩረት ሰጥተነው ስንተገብር በብዛት አንታይም በግብጽ ቤተክርስቲያን የምክክር አገልግሎት ተቋም እንደተደራጀ እና ካህናትም በቤተክርስቲያን  መርሐ ግብር ተመድቦላቸው ለረጅም ሰዓት ሲመክሩ እንደሚውሉ ምሥክሮች ይናገራሉ ቢቻለን በሰ/ት/ቤቶችና በስብከተ ወንጌል ክፍሎች ውስጥ እንደዚሁም መንፈሳዊ አገልግሎት ሰጪ ማኅበራት መንፈሳዊ የምክክር አገልግሎት ክፍሎች አቋቁመን ካህናት አባቶች እና በምክክር ደረጃ ወደ ካህናት ሊያደርሱ የሚችሉ ጸጋው እና ችሎታው ያላቸው አገልጋዮች በማሳተፍ ብንተጋ ለቤተክርስቲያን  ሆነ ለሐገራችን መልካም ፍሬ እናፈራለን እንደዚሁም አደራችንን በመወጣት መንፈሳዊ ዋጋ እንደምናገኝበት የታመነ ነውና፡፡ “የሚመክር ቢሆን በመምከሩ ይትጋ” ሮሜ 12፣6-8



ምክክርና መንፈሳዊ የምክክር  አገልግሎት ምንነት

በሰው ልጆች ኑሮ ውስጥ ሃዘንና  ደስታ መከሰታቸው የማይቀር ነው በእያንዳንዱ የእድገት ዘመናችን የተለያዩ ችግሮች በተፈጥሮአዊና በአካባቢያዊ ምክንያት ያጋጥመናል፡፡ ለችግሩም ቶሎ መፍትሄ ካልፈለግን በጤና በሥራ በማኀበራዊ እና መንፈሳዊ ኑሮአችን ላይ ተጽዕኖ ያመጣብናል፡፡ በመሆኑም  ችግራችንን አስወግደን ጤናማ ኑሮ ለመምራት  አንዱ መፍትሄ ምክክር ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍም የምክክር አገልግሎት እንመለከታል፡፡





ምክክር ምንድነው?

ምክክር እንደ ሥነ- ልቦና የምሁራን አገላለጽ ለአንድ ወይም ከዚያ በላይ ለሆኑ ሰዎች ለችግራቸው በጋራ መፍትሄ ለመፈለግ የሚደረግ ውይይት (ግንኙነት) ነው፡፡

ምክክር ሰዎች በተፈጥሮ በትምህርትና በልምድ ያገኙትን አቅም በአግባቡ መጠቀም ችግሮች እንዳይገጥማቸው በመከላከልና የሚገጥማቸውንም ችግሮች ለመቋቋም ለራሳቸውና ለወገናቸው ትርጉም ያለውን ሥራ እንዲሰሩና ሕይወታቸው የተሳካ እንዲሆን መረዳት ወይም ማገዝ ነው፡፡ በአጠቃላይ ሰዎች ችሎታቸውን እንዲያውቁና እንዲያሳድጉ የሚያስችል ነው፡፡ በምክክር አገልገሎት ውስጥ ምክክርን የሚመራው “አመካካሪ” ሲባል መፍትሄ ፍለጋ የመጣው “ተመካካሪ” (Cliant) በመባል ይታወቃል፡፡

የምክክር አገልግሎት ላይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው አመካካሪው የተመካካሪውን ችግር ከነመንስዔው አጣርቶ ተመካካሪው እራሱ ችግሩን ከአመካካሪው የሚደረግለት እገዛ ተጠቅሞ ውሳኔ ላይ እንዲደርስ ማድረግ ነው፡፡

የምክክር ግብ

እንደ መስኩ ባለሞያዎች አገላለጽ ምክክር ጠንካ ግብ ያለው መሆኑን በመግለጽ የሚከተሉት መሆናቸውን ያስገነዝባሉ፡፡

  • ተመካካሪው በደረሰበት ችግር የጠባይ ለውጥ እንዲያመጣ ሁኔታዎችን ማመቻቸት፣
  •         የችግር መቋቋሚያ ዘዴዎችነ እንዲያዳብር ማድረግ፣
  •        ተመካካሪው እምቅ እውቀቱንና አቅሙን መጠቀም እንዲችል ማበረታታት፣
  •        ተመካካሪው በራስ መተማመንን እንዲያዳብር መርዳት እራሱን እንዲሆን ማድረግ እና የመሳሰሉት ግቦች ያሉት ነው፡፡



የምክክር ዓይነቶች

     ምክክር ከሥነ- ልቦና ትምህርት አንዱ ክፍል ሲሆን ዓይነቶቹም በርካታ ስለመሆናቸው ምሁራን ይገልጻሉ፡፡ ከእነሱም ውስጥ፡-

·         የ ቤተሰብ ምክክር አገልግሎት (የቤተሰብ አባላት ባሉበት) ሊደረግ የሚችልና ችግራቸው እንዲፈታ

·         የማማከሪያ ሂደት ነው፡፡

·         የጋብቻ ምክክር

·         የወጣቶችና የሕጻናት ምክክር

·         የአካል ጉዳተኞች ምክክር

·         የውሳኔ አሰጣጥ ምክክር

·         የትምህርት ምክክር

·         የሥራና የሞያ ምክክር የሐዘን ምክክር

·         የኤች. አይ.ቪ/ኤድስ ምክክር

·         የመንፈሳዊ ምክክር አገልግሎት

    የዚህ ጽሑፍ ዓላማ የምክክር ምንነት ለመጠቆምና የመንፈሳዊ ምክክር አገልግሎትን ለመግለጽ በመሆኑ በመንፈሳዊ የምክር አገልግሎት ላይ እናተኩራልን፡፡

ይቀጥላል.......



















2 comments:

  1. በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
    “የሚመክር ቢሆን በመምከሩ ይትጋ” ሮሜ 12÷6-8
    አባታቸን፣ ወንድማችን እና አገልጋያችን ቀሲስ ፋሲል ታደሰ በእርሶ በኩል ለህዝበ ክርስቲያኑ እያበረከቱን ያለው እገዛ፤ ፈጣሪ አምላክ መድኃኒዓለም በበረከትና በጸጋው ይጎብኞት ማለት እፈልጋለሁኝ፤ በእውነት የእኛን የወጣቶችን ህይወት በቃሉ የተቃና ለማድረግ እየሰጡ ያሉት አገልግሎት በምድርም ሆነ በሰማይ ፍጹም ዋጋ ያለውና በቃላት የሚገለጽ ትርፍ አይደለምና እግዚአብሔር እንደ እርሶ ያሉ ዘመኑን የሚዋጁ አገልጋዮችን ያብዛልን ስል ፍጹም ከውስጤ ነው፡፡
    ይህ የእርሶ አገልግሎት ለሌሎችም የቤ/ክ አባቶችና አገልጋዮች አርዓያ ስለሚሆን፣ ከሚመለከታቸው የቤተክርስቲያኒቷ አስተዳደር ጋር በመነጋገር በሁሉም አገልጋዮች ዘንድ እንዲዘወተር እንዲሁም የአንድ የቤ/ክ አገልጋይ ኃላፊነት እና ግዴታ መሆኑን እንዲታወቅና የልምድ ልውውጥ እንዲኖር የዘወትር ጠንካራ ትጋቶን እንጠይቃለን፡፡
    ከዚህ ውጭ አሁን አዲስ የከፈቱት ድህረ ገጽ (ዌብ ሳይት) ላይ በ face book, twitter, .. ፣ ሌሎችም like, Share, Print, e-mail, Join, የሚሉ በተኖች (ዝርዝር ሜኖዎች) ቢኖሩት አገልግሎቱን ለሌሎችም ለማስተዋወቅ እና ብዙ የድህረ ገጹን አባል ለመፍጠር አስፈላጊ ስለሆነ ቢጨመርበት፡፡ በተጨማሪም የሌሎች ኦርቶዶክሳዊ ዶግማና ቀኖናን የጠበቁ ድህረ ገጽ አድሬሶች ዝርዝር ቢኖረው ተገልጋዩ በቀላሉ ከእርሶ ድህረ ገጽ ተነስቶ ተጨማሪ መረጃ ማግኘት ይችላል፤
    ከዚህ ውጭ እጅግ አስደሳች ጅምር ነው፣ ተጠናክሮ ይቀጥል፡፡
    ቃለ ህይወት ያሰማልኝ!!!
    ተክለ ጻዲቅ
    ከአዲስ አበባ፤

    ReplyDelete