Tuesday 10 September 2013

5ቱ ስጦታዎች (ክፍል 2)

4.በኩራት
በኩር ማለተ የመጀመሪያ ማለት ሲሆን የበኩራት ስጦታ ከልጅ፤ከከብት፤ከንብረት… ከመሳሰለው የመጀመሪያውን መስጠት ነው፡፡የአዳም ልጅ አቤል መስዋዕት ሲያቅርብ ‹‹ የመጀመሪያውን ለየ›› የሚለው በኩራቱን ስለማቅረቡ ሲያስረዳ ሲሆን፡ ይህም የተወደደ መሥዋዕት ሆኖለታል /ዘፍ 4፤4/ ፡፡ከዘመነ ኦሪት ጀምሮ ሕዝበ እግዚአብሔር  አምልኮታቸውን ከሚገልጹበት አንዱ በኩራት ነበር፡፡ከልጆቻቸው፤ከምርታቸው.... በኩር  የሆነውን ለእግዚአብሔር ቤት ይሰጣል፡፡ /ዘኁ 3፤42፤ 1ሳሙ 2፤ ዘኁ 18፤15-17/፡፡
በኩራትን ማቅረብ እጅግ የተወደደ እና ከሁሉ የሚበልጥ የስጦታ ዓይነት ነው /ዘዳ.23÷19፤ ዘዳ.26/፡፡ክርስቲያኖችም ሁላችንም ሥርዓተ አምልኮ የምንገልጥበት አንዱ የሆነውን በኩራቱን በማቅረብ ሕገ አምላክን ልንጠብቅ ይገባል፡፡ይህንንም ከመጀመሪያ ምርታችን፡ ከመጀመሪያ ደሞዛችን ለእግዚአብሔር ቤት በመስጠት የተናገረውን ከማያስቀረው አምላካችን በረከት እንደምናገኝ በማመን ልንፈጽም ይገባናል /ዘዳ28÷1-15/፡፡
5.ዐሥራት
ዐሥራት አንድ አሥረኛ ማለት ነው፡፡ከሚያገኙት ገቢ አንድ አሥረኛውን ለእግዚአብሔር ቤት መስጠትን ያመለክታል፡፡ከሙሴ በፊት በዘመነ አበው የተጀመረ የእግዚአብሔር ሕግ ነው፡፡መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዐሥራት በስፋት ይገልጻል፡፡ከነዚህም ለአብነት ያህል በጥቂቱ እንመልከት፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዐሥራት አበ ብዙሓን አብርሃም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ወደ መልከ ጼዴቅ በሄደ ጊዜ ዐሥራት ማውጣቱን ‹‹አብርሃምም ከሁሉ ዐሥራት ሰጠው›› በማለት ዐሥራትን አበው እነደጀመሩት ያስረዳናል/ዘፍ 14÷20/፡፡ ያዕቆብ ከአባቶቹ የወረሰውን ሕገ አምላክ የሆነውን ዐሥራት ማውጣትን ሲገልጽ ‹‹ከሰጠኸኝ ሁሉ ለአንተ ከዐሥር አንዱን እሰጣለሁ›› ብሏል /ዘፍ 28÷ 1-22/፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዐሥራት ሲያስረዳን ከእግዚአብሔር የታዘዘ መሆኑን አጽንኦት በመስጠት  ነው፡፡ ‹‹ከምታገኘው ሁሉ ዐሥራትን ታወጣለህ›› የሚለው ‹‹ዐሥራት አስገቡ›› ማለቱ እነደዚሁም የምድር ዐሥራት የእግዚአብሔር መሆኑን የሚገልጹ ማስረጃዎች ሁሉ ዐሥራት ሕገ አምላክ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ /ዘዳ. 14÷22፤ ዘሌ.27÷30፤ ዘዳ.12÷17፤ ዘዳ.14÷23፤ ሚል.3÷10/፡፡
መድሓኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በመዋዕለ ስብከቱ ‹‹የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ስጡ›› ማለቱ አምላካዊ ትዕዛዝ መሆኑን ያስገነዝበናል /ማቴ 22÷17/፡፡እንደዚሁም አንድ ቀራጭ ወደ ጌታችን ቀርቦ ‹‹ከማገገኘው ዐሥራት አመጣለሁ›› ማለቱ ቀድሞ የነበረ ሕግ መሆኑን የሚያመለክት ሲሆን ጌታችንም ቀራጩን በዐሥራት ጉዳይ ላይ መልስ አለመስጠቱ ዐሥራት ተገቢ የሆነ ሥርዓት መሆኑን የሚያመለክት ነው /ሉቃ 18÷12/፡፡

ዐሥራት በመስጠታችን የምናገኘው ጥቅም ምንድን ነው?