Thursday 18 July 2013

ምክረ ካህን



“መፋታትን እጠላለሁ ”ሚል 2÷16

ጋብቻ እግዚአብሔር የፈቀደው ክቡር ነው በይበልጥም በስርዓተ ቤተክርስቲያን በንስሐ እና በቅዱስ ቁርባን የሚፈፀም ጋብቻ ቅዱስ ጋብቻ ነው፡፡ ኤፌ 5÷32 ማቴ 19÷5 ሆኖም ግን ጋብቻ የበዛውን ያህል ፍቺም እየበዛ መሆኑ ግልፅ ነው በርካቶችም ወደ ፍቺ የሚያመራ ትዳር ውስጥ እንደሚገኙ ይናገራል ስለሆነም በዚህ እትም በምክረ ካህን ዓምድ የፍቺ ምክንያቶችና ፍቺ እንዳይገጥም መፍትሔዎችን በጥቂቱ እናስነብባለን፡፡
እግዚአብሔር ፍቃዱ በጽናት እንድንኖር ነው እንጂ ፍቺን እንደሚጠላ “መፋታትን እጠላለሁ” የሚለው አምላካዊ ቃል ያስረዳናል፡፡ ከጋብቻ በፊት የመጠናናት ዓላማ ክፉ፣ደግ ጠባያቸውን ለይተው ተቻችለው ለመኖር መሰረት የሚጥሉበት ነው፡፡ ሆኖም ግን አንዳንዶች በአግባቡ ሳይጠናኑ ወይም ስለ ጋብቻ ኑሮ በቂ ግንዛቤ ሳይኖራቸው ወደ ትዳር ሲገቡ ከመኖር ይልቅ ፍቺ ሲገጥማቸው ይታያል በርግጥ በዝሙትና በሀይማኖት ልዩነት ፍቺ ሊኖር እንደሚችል ይታወቃል ከተስተካከሉ ወይም ችግራቸውን ካስወገዱና ከተስማሙ ከፍቺው ይልቅ አብሮ መኖር የተመረጠ ነው፡፡ ሉቃ 16÷18   ማቴ 19÷9
በዘመናችን በርካቶችን ለፍቺ የዳረጉ ነገሮች ምን ይሆኑ?

Friday 12 July 2013

ነገር በምሳሌ….



በግ በውሻ ቀና
ሊቁ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ስኳርና ወተትየሚል ከእንግሊዘኛ የተተረጎመ በ1922ዓ.ም ከፃፉት ተረት መጽሐፍ ላይ የጠቀሱትን እንመልከትና እንማርበት፡፡ ምሳሌ ማስተማሪያ መንገድ ነው፡፡
ብዙ በጎች ያሉት አንድ ሰው ነበር እርሱም በጎቹን ሲጠብቅ በብዙ ጥንቃቄ ነው፡፡ የለመለመ ሳር ይመግበቸዋል፣ የጠራ ውሃ ያጠጣቸዋል ሲመሽም ወደ ጉሮኗቸው ያስገባቸዋል፡፡ በዚህ መልኩ በጣም ይንከባከባቸዋል፡፡ ከአንዱ ግልገል በቀር ሁሉም ጠባቂያቸውን ይወዳሉ፡፡ ያ አንዱ ግልገል ግን ጠባቂውን አይወድም፡፡ አንድ ቀን ወደ እናቱ ቀርቦ እናቴ ሆይ እኛ ማታ ማታ ለምን ይዘጋብናል እነሆ ውሾች ሳይዘጋባቸው እየተጫወቱ ያድራሉ፡፡ እኔም ከአሁን በኃላ እንደ ውሾች ማታ ማታ መጫወት እፈልጋለሁኝአላት፡፡ እናቲቱም ልጄ ሆይ አርፈህ ተቀመጥ ጠባቂያችን እጅግ መልካም ነው እርሱ እንዳዘዘን ውለን ብንገባ ይሻለናል፡፡ እንቢ ያልክ እንደሆነ በራስህ ላይ ጥፋት ታመጣለህ አለችው፡፡ 

ሐዋርያት



ሐዋርያ የሚለው ስያሜ ሖረ፣ሔደ ከሚለው ከግዕዝ ግስ የወጣ ሲሆን ትርጉሙ የተላከ፣ሒያጅ፣ልዑክ ማለት ነው፡፡ ይህ መጠሪያ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማስተማር ዘመኑ ከተለያዩ ተግባራት እንዲከተሉት ከጠራቸው ለ12 ደቀ መዛሙርት የተሰጠ ስያሜ ነው፡፡ ማር 3÷13 በኃላም ወንጌልን እንዲሰብኩ “ሑሩ ወመሐሩ” ብሏቸዋልና ሐዋርያት ተባሉ፡፡ ማቴ 28÷19 ቅዱሳን ሐዋርያትም ከድሆች፣ ከሀብታሞች፣ ከምሁራን፣ ካልተማሩ ወገኖች ሲመርጥ ለዓለምም ክብር እንዲያጎናጽፉ የበረከት መልዕክተኞች የዓለም ጌጦች አድርጓቸዋል፡፡


Tuesday 2 July 2013

እየሩሳሌም


            “እየሩሳሌምን በልባችሁ አስቡ” ‹‹.ኤር 51÷51››
ነቢዩ ኤርምያስ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ539 ዓ/ዓለም ገደማ ስለኢየሩሳሌም ነፃ መውጣት እና ስለ ባቢሎን መፍረስ የተናገረው ነው፡፡ ፍፃሜውም በኢየሩሳሌም ስለሚፈጸመው ነገረድኅነት እና ከክርስቲያኖች ልብ የማትጠፋ ሀገር ስለመሆኗ የሚያመለክት ነው፡፡
እስራኤል
አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር ለይስሐቅ ልጅ ለያዕቆብ የሰጠው ስያሜ ነው፣ ካልባረከኝ አልለቅምህ ብሎ ነበርና “ከእግዚአብሔር ጋር ይታገላል ያሸንፋል” ሲል እስራኤል አለው፡፡ ዘፍ. 32÷22 በኋላም የያዕቆብ ልጆች የተጠሩበት እና ከሰሎሞን በኋላ ዐሥሩ ነገዶች ያቋቋሙት የሰሜናዊው ግዛት (መንግሥት) ስያሜ ሆኗል፡፡ ዘፍ 49÷7 ዘዳ 14÷39 1ኛ ነገ.12÷16
 በአዲስ ኪዳን የክርስቶስ ተከታዮች እስራኤል ዘነፍስ ተብለዋል ሮሜ. 9 ገላ. 3÷6 ሮሜ. 4÷12
እየሩሳሌም
ኢየሩሳሌም ማለት መሠረት ሠላም፣ ሀገረ ሠላም፣ የሠላም ምልክት…. ማለት ነው፡፡ ስትጠራም የእግዚአብሔር ከተማ፣ ቅድስት ከተማ፣ የዳዊት ከተማ ተብላ በቅዱሳት መጻሕፍት ተጠቅሳለች ንጉሠ ሰላም የተባለው የጌታችን ምሳሌ ሆኖ የሚነገረው መልከፄዴክ እንደመሠረታት ይነገራል፡፡ ዘፍ. 14÷ ነህ. 11÷1 የአበ ብዙኃን አብርሃም የልጆቹ፣ የበርካታ ነቢያት ሀገራቸው ፣ ታላቁ ንጉሥ ቅዱስ ዳዊትም ከኢያቡሳውያን ማርኮ ከተማው ያደረጋት በመሆኗ የነቢያት ትንቢት ፍፃሜ አግኝቶ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከልደት እስከ ዕርገት የኖረባት፣ ሐዋርያት የተጠሩባት፣ ነገረድኅነት የተፈፀመባት በመሆኗ በእውነትም ቅድስት ሀገር ናት፣ በማዕከለ ኢየሩሳሌም ጽርሐጽዮን የሰሎሞን ቤተመቅደስ፣ ከጲላጦስ አደባባይ እስከ ቀራንዮ መከራ መስቀል የተቀበለባቸው ቦታዎች ይገኛሉ፡፡