ገዳማትወአድባራት



ጽርሐ አርያም ቅዱስ ሩፋኤል
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሚገኝ ደብር። የተተከለው በዐፄ ምኒልክ ዘመነ መንግስት በ1874 ዓ.ም ቃልየ ከሚባል ተረተር ከፍተኛ 8 ቀበሌ 05 ውስጥ ነበር። ነገር ግን ብዙ ተቃዋሚዎች ስላስቸገሩ /እንደ አንዳንዶቹ ደግሞ በመብረቅ ስለ ተቃጠለ/ ታቦቱ ከዚያ ተነስቶ ከዑራኤል ቤተ ክርስትያን ታቦት ጋር ተዳብሎ ለ 16 ዓመታት ፣ከዚያም በጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን ለአንድ ዓመት ከቆየ በኃላ በጳጉሜን ሦስት ቀን 1902 ዓ.ም በልጅ ኢያሱ ትእዛዝ በራስ ቢትወደድ ተሰማ አሳሳቢነት አሁን ያለበት ስፍራ (ጉለሌ ክፍለ ከተማ በተለምዶ እንቁላል ፋብሪካ ከሚባለው አካባቢ ወደ ላየ) የዐፄ ምኒሊክ መናፈሻ ቤት /ንጉሡ ለዒላማ ተኩስ፣ለንጉሥ ጨዋታና ለግልቢያ ወደ ጉለሌ ሲመጡ የሚያርፉበት/ ስለ ነበረ እርሱ ተፈቅዶ ታቦቱ እዚያ ገባ። ዛሬም ያ መናፈሻ ለሰንበቴ ማኀበር እያገለገለ ነው።
    በንግሥተ ነገስታት ዘውዲቱ ዘመነ መንግስት ዛሬ የሚገኘው ሕንጻ ተሠራ። ቤተ ክርስቲያኑን ያሠሩት ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ሲሆኑ የቆርቆሮ ክዳን ያለበሱት እቴጌ መነን ናቸው። የደብሩን ሥዕል የሣሉት አለቃ ገብረ ሥላሴ እና አለቃ መዝሙር ዘዳዊት ናቸው።
  በጣልያን ወረራ ጊዜ እነ ደጃች አበራና አቡነ ጴጥሮስ በዚያ በኩል በመምጣታቸው የተነሣ ተባብራችኃል በሚል የተወሰኑ ካህናት ጣልያን በቦንብ ረሸናቸው። የጣልያን ወታደርም ቤተ ክርስቲያኑን በዓይነ ቁራኛ መጠበቅ ጀመረ። በኃላ አንድ የጣልያን ወታደር በወረወረው ሲጋራ ዕቃ ቤቱ የገና እለት ተቃጠለ። አቡነ ጴጥሮስ ለሰማዕትነት ወደ አዲስ አበባ ከመግባታቸው በፊት በዚህ ቤተ ክርስቲያን ጸሎት አድርገው ነበር። በዚያ የምትገኘውንም ታቦተ ኪዳነምሕረት እርሳቸው እንዳመጡት ይነገራል። በየካቲት 12 ቀን የአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ በጣሊያን ሲያልቅ ጣሊያኖች ብዙ ሬሳ በመኪና ጭነው መጥተው ካህናቱን በኃይል ጉድጓድ በማስቆፈር በደብሩ ዙርያ በጋራ መቃብር ቀብረቃቸዋል። በደብሩ ብላቴን ጌታህሩይ የተክለ ጻዲቅ አባት ደብተራ መኩሪያ ፤ ታላቁ ሊቅ አለቃ ይትባረክ መርሻ. . . የመሳሰሉ ሊቃውንት አገልግለውበታል በዚህም ወቅት በርካታ ሊቃውንት የሚገኙበት ጾመ ድጓ የሚቆምበት ፤ ዘወተወር የሚቀደስበት አንጋፋ ደብር ሲሆን የእግዚአብሔር ፤ ኪዳነምሕረት ፤ ነብዩ ኤልያስ ታቦታት ይገኙበታል።

https://blogger.googleusercontent.com/img/b/R29vZ2xl/AVvXsEjxsRlR3upn8rCRMq4MEQ6Gx99LWhwJ-OBX_kd-SFmh00kBkL0RM-zhYnu5rGFVI7AYqpgHmaLuevZBUgbZdas-1jA_VtbxPBwmmb4U0w1xcET0AsthJl6QjPgWmOYimB48I5OK8pWeCrVS/s1600/rufael.jpg

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/ የናየሮቢ ደብረ መድኃኒት መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስትያን

  በ1976 ዓ.ም. በናይሮቢ በተለያየ ምክንያት ገብተው ሲኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን በመሰባሰብ እና በመመካከር መንፈሳዊ በረከት ፍለጋ ተነሡ። በወቅቱ በከተማው ከሚገኙት የግብጽ ጳጳሳት አቡነ ማርቆስ ቤት በመሄድ እንዲያስተምሩአቸው ጠየቁ አቡነ ማርቆስም በቤታቸው እያስተማሩአቸው እና ልጆቻቸውንም ክርስትና እያነሡላቸው ቆዩ ኢትዮጵያውያን ምእመናን ሲበራከቱ ግቢው ውስጥ ጊዜያዊ ሰፋ ያለ መሰባሰቢያ ሠሩ። የቤተ ክርስቲያናችን ቅዳሴ እና እጣን. . ሲናፍቃቸው ጳጳሱን አማክረው ከኢትዮጵያ አባቶች ለማስመጣት አቀዱ ጉዳዩ ተሳክቶ አቡነ ኤልያስ እና አባ ገብረ ሥላሴ (የአሁን አቡነ አረጋዊ) ተገኝተው ባረኳቸው።
አቡነ ኤልያስ በምዕመኑ ትጋት ስለተደነቁ ለነሐሴ እንሚመለሱ ቃል ገቡ ጊዜው ደርሶ ሲመለሱ አቡነ ማርቆስ ወደ ግብጽ በሄዱበት አጋጣሚ ሆነና ሌሎቹ ኃላፊዎች ቦታውን ከለከሉ ፤ አዳራሽ በመከራየት አባቶቹ አገልግሎቱን አከናወኑ ፤ በተከራዩትም ሶስት ወር ተገለገሉ። ብፁዕ አቡነ ኤልያስ ኢትዮጵያ ተመልሰው ለቅዱስ ፓትርያርኩ ለአቡነ ተክለሃይማኖት ሁኔታውን ሲያስረዱ በሁኔታው ያዘኑት ቅዱስነታቸው ለቤተ ክርስትያን ቦታ መግዣ 100 ሽህ ዶላር ላኩ ገንዘቡን የተረከቡት ትጉሃን ምእመናን አሁን የሚገኝበትን ቦታ ገዝተው በመጠነኛው ቤተ መቅደስ አገልግሎቱን አስፋፍተዋል። በእግዚአብሔር ፈቃድ በምእመናኑ ብርታት ታህሣሥ 8,1997 ዓ.ም. በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ተባርኮ መስረቱ የተጣለው ህንጻ ፍጻሜው መስከረም 21 1999 ዓ.ም ሆኖ ቅዳሴ ቤቱ ተከብሯል። እንሆ ዘንድሮም በርካታ ኢትዮጵያውያን እየተገለገሉ በረከተ ነፍስ ወስጋ እያገኙ ነው። በደብሩ ዘውትር ኪዳን በበዓላት እና በሰንበት ቅዳሴ ሲኖር የቅዱስ ገብርኤል እና ታቦተ ማርያም ይገኛሉ።

https://blogger.googleusercontent.com/img/b/R29vZ2xl/AVvXsEiArBsXg2-SlcM9TX7XFMbK1732p5ozYTECWBYnmrB6jqOnttz6UmNhVfgY9umh_KJKw6dDML5yR6X7TzByvZu0E7-RQrHPHSKpPUcdnpcmEg70dTQfwrEMPNlCAGiSxuwP_Gji2mQ-REuc/s320/Nairobi+Medhanialem.jpg



No comments:

Post a Comment