Thursday 22 August 2013

5ቱ ስጦታዎች

ሥርዓተ አምልኮ ከሚገለጥበት መንገድ አንዱ ስጦታ ነው፡፡ የሰው ልጅ ከራሱ የሆነ አንዳች የለውም በጎ የሆነው ሁሉ ከፈጣሪ ዓለማት ከእግዚአብሔር ያገኘው ነው፡፡ በመሆኑም ፈጣሪያችን መስጠትን እንዳስተማረን ሁሉ እኛም ተገዥነታችንን ከምንገልጥበት አንዱ ከርሱ የተቀበልነውን በፈቃደኝነት በደስታ በመስጠት ነው፡፡ ነቢዩ ዳዊት ይህን ሲያስረዳ ‹‹ሁሉ ከአንተ ዘንድ ነውና፡ ከእጅህ የተቀበልነውን ሰጥተንሃልና ይህን ያህል ልናቀርብልህ የቻልን ማነን? .. በፈቃዴ ይህን አቅርቤአለሁ›› በማለት ከእግዚአብሔር ያገኘውን ሀብት በደስታ በፈቃዱ ለቤተ መቅደስ ሥራ እንዲውል መስጠቱን በመግለጽ ስለ ስጦታ ጽፏል /1ዜና 29÷9-16/.
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ነገር ግን ሁሉ በአግባብና  በሥርዓት  ይሁን›› በማለት እንዳስተማረን ለእግዚአብሔር የምንሰጠውን የአምልኮ መግለጫ በሥርዓት ልናደርገው እና ከልብ  ሊሆን ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ መሠረቱ  የስጦታ ዓይነቶችንና የአቀራረብ ሥርዓቱን ማወቅ ነው፡፡በዚህች አጭር ጽሑፍም በሥርዓተ ቤተክርስቲያን መሠረት መንፈሳዊ ምግባራት የሆኑት አምስቱ የስጦታ ዓይነቶች ምጽዋት፡ መባዕ፡ ስዕለት፡ በኩራት እና ዐሥራትን እንመለከታለን፡፡