Thursday 22 August 2013

5ቱ ስጦታዎች

ሥርዓተ አምልኮ ከሚገለጥበት መንገድ አንዱ ስጦታ ነው፡፡ የሰው ልጅ ከራሱ የሆነ አንዳች የለውም በጎ የሆነው ሁሉ ከፈጣሪ ዓለማት ከእግዚአብሔር ያገኘው ነው፡፡ በመሆኑም ፈጣሪያችን መስጠትን እንዳስተማረን ሁሉ እኛም ተገዥነታችንን ከምንገልጥበት አንዱ ከርሱ የተቀበልነውን በፈቃደኝነት በደስታ በመስጠት ነው፡፡ ነቢዩ ዳዊት ይህን ሲያስረዳ ‹‹ሁሉ ከአንተ ዘንድ ነውና፡ ከእጅህ የተቀበልነውን ሰጥተንሃልና ይህን ያህል ልናቀርብልህ የቻልን ማነን? .. በፈቃዴ ይህን አቅርቤአለሁ›› በማለት ከእግዚአብሔር ያገኘውን ሀብት በደስታ በፈቃዱ ለቤተ መቅደስ ሥራ እንዲውል መስጠቱን በመግለጽ ስለ ስጦታ ጽፏል /1ዜና 29÷9-16/.
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ነገር ግን ሁሉ በአግባብና  በሥርዓት  ይሁን›› በማለት እንዳስተማረን ለእግዚአብሔር የምንሰጠውን የአምልኮ መግለጫ በሥርዓት ልናደርገው እና ከልብ  ሊሆን ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ መሠረቱ  የስጦታ ዓይነቶችንና የአቀራረብ ሥርዓቱን ማወቅ ነው፡፡በዚህች አጭር ጽሑፍም በሥርዓተ ቤተክርስቲያን መሠረት መንፈሳዊ ምግባራት የሆኑት አምስቱ የስጦታ ዓይነቶች ምጽዋት፡ መባዕ፡ ስዕለት፡ በኩራት እና ዐሥራትን እንመለከታለን፡፡


1.ምጽዋት፡-
ምጽዋት መስጠት ከገንዘብ፡ ከዕውቀት ፡ ከንብረት… ላይ  ለእግዚአብሔር ቤት መለገስ ነው፡፡ መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በአንቀጸ ብጹአን ትምህርቱ ‹‹ብጹዓን መሐርያን ፡ የሚምሩ ብጹአን ›› ናቸው ያለውን ለምጽዋት ሰጥተውት ሊቃውንት ሲተረጉሙት በሦስት መንገድ ያስቀምጡታል፡፡ እነዚህም፡-
ሀ/ምህረት ሥጋዌ፡- ይህ የሚያስረዳው ለሥጋ የሚሆን ነገርን መለገስን ሲሆን
ለ/ምሕረት መንፈሳዌ፡- በምክር፡ በትምህርት…. ሥነ ልቡናን የሚያንጽ (የሚያበረታታ) ማድረግን ነው፡፡
ሐ/ምሕረት ነፍሳዊ፡- ደግሞ ራስን እስከ መስጠት ‹‹መጥወተ ርእስ›› መድረስን ነው /ማቴ 5÷7 ትርጓሜ ወንጌል/፡፡
ምጽዋት ካለን ነገር ላይ ማካፈልን ያመለክታል፡፡ለፍጹምነትም የሚያበቃ ምግባር መሆኑ የተመሰከረለት ነው፡፡‹‹ ፍጹም እንድትሆን ለድሃ ስጥ›› እንዲል /ማቴ 19-21/፡፡‹‹የሚሰጥ ብጹዕ ነው›› የሚለውም ሃይለ ቃል ይህን ያስረዳል፡፡/ሐዋ 20÷35/፡፡ በነገረ ምጽአትም ከሕይወት ቃል አንዱ በምጽዋት የሚገኝ መሆኑ እሙን ነው /ማቴ.25-35/፡፡
ምጽዋትን በልብስ፡ በገንዘብ፡ እንጀራ በመቁረስ የመሳሰሉትን ለደሃ በመስጠት፡ በማካፈል መግለጽ ይቻላል፡፡ በእየሩሳሌም የሚኖሩ ምእመናን ሀብታቸውን ለደሃ ያካፍሉ ነበር /ሐዋ 4÷32 6÷1-6/፡፡እንደዚሁም እውቀትን ማካፈል፡ ምክር መለገስ ከምጽዋት የሚቆጠር ሲሆን ፡ ለእግዚአብሔር ቤትም በገንዘብ፡ በጉልበትና በስጦታችን ማገልገል የምጽዋትን ዋጋ ያስገኛል /ኢሳ 58÷7 ፡ ሮሜ 12÷8 ፡ ዘዳ. 15÷11-15 ፡ ምሳ 3÷27/፡፡ በረከተ ሥጋ ወነፍስ የሚያስገኘውንና በደልን የሚያስወግደውን የልግስና  ስጦታ /ምጽዋትን/ ልማዳችን ማድረግ ይገባናል /ዳን. 4÷27/፡፡
2.መባዕ፡-
ለአምላካችን ለልዑል እግዚአብሔር ከሚቀርቡ የስጦታ ዓይነቶች አንዱ መባዕ ነው/ ዘሌ 1÷3፡ ዘኁ.7÷12/፡፡ ነቢዩ ዳዊት መባ ለእግዚአብሔር ቤት እንደሚገባ ሲገልጽ ‹‹እበውእ ቤተከ ምስለ መባእየ፡ መባዬን በመያዝ ወደቤትህ እገባለሁ›› ብሏል /መዝ 65÷13/፡፡ መባዕ ለቤተመቅደስ መገልገያ የሚሆንና ንዋያተ ቅድሳትን በመስጠት የሚፈጸም ሲሆን ለምሳሌ ጧፍ፡ ዕጣን፡ ዘቢብ፡ … የመሳሰሉት በአጥቢያችን እና በተለያዩ ገዳማት ስንሔድ ይዘን መግባት ይጠበቅብናል፡፡ /ዘዳ. 13÷35 ፡ 34÷20/፡፡
መባዕ ማቅረብ የተገዥነት መገለጫ በመሆኑ በረከት የሚያስገኝ ምግባር ነው፡፡ በቤተክርስቲያንም በጸሎተ መባዕ በካህኑ በሚደርስው ሥርዐተ ጸሎት መሠረት የመንፈሳዊ ጸጋ ተሳታፊ ያደርጋል /ማቴ. 5÷24 ፡ ማር 7÷10-12/፡፡
3.ስዕለት፡-
ስዕለት  ሰው በፈቃዱ አንድ ነገር ለእግዚአብሔር ለማድረግ /ደስታውን ለመግለጥ/ ቃል የሚገባበት ሥርዓት ነው፡፡ በእግዚአብሔር ቸርነት በቅዱሳን አማላጅነት  በማመንና በመማጸን ‹‹ ይህ ቢደረግልገኝ ይህን አደርጋለሁ›› በሚል አገላለጽ ቃል የሚገቡበት የስጦታ ዓይነት ነው፡፡ ስዕለት እምነታችንን የምንገልጽበትም በመሆኑ በሥርዐት እና ከልብ ሆነው ስእለት ሊሳሉ ይገባል፡፡ ጠቢቡ ሰለሞን ይህን‹‹ ለእግዚአብሔር በተሳልህ ጊዜ ትፈጽመው ዘንድ አትዘግይ፡ የተሳልከውን ፈጽም፡የማትፈጽም ከሆነ አትሳል›› በማለት አስረድቶአል/መክ 5÷4/፡፡ እመሳሙኤል ሐና እንደተሳለችና ስእለቷን እንደፈጸመች ይህም ምግባር ቀድሞ የነበረና መጽሐፍ ቅዱሳዊ እንደሆነ የሚያስተምረን ነው/ 1ገኛ ሳሙ.1-1/፡፡ በረከት ለመቀበልና ፍላጎታቸው እንዲሟላ የሚሳሉም ነበሩ፡፡/ዘፍ. 28÷20 ፡ ዘሌ 20 7 ፡ ዘኁ. 21÷1-3፡ መሳ. 11÷30/፡፡
ስእለትን በአግባቡ መሳል እና በቃላችን መሠረት መፈጸም የሚገባ ሲሆን ነገር ግን ቃልን አለመጠበቅ ደግሞ ኃጥያት ስለመሆኑ እንዲህ ተጽፏል ‹‹ለአምላክህ ለእግዚአብሔር  ስእለት በተሳልህ ጊዜ አምላክህ እግዚአብሔር  ከአንተ ፈጽሞ ይሻዋልና ኃጥያትም ይሆንብሃልና መክፈሉን አትዘገይ፡፡ ባትሳል ግን  ኃጥያት የለብህም በአፍህ የተናገርኸውን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር በፈቃድህ ተስለሃልና ከከንፈርህ የወጣውን ታደርግ ዘንድ ጠብቅ›› /ዘዳ. 23÷21-23፡ ምሳ. 20÷25/፡፡

ይቀጥላል…..

8 comments:

  1. ቃለ ህይወት ያሰማልን

    ReplyDelete
  2. ketlubet teru tsehuf new

    ReplyDelete
  3. Kesis Burakehi yidireseni.

    We are waiting the next article.
    Be God with your service.

    Bye

    ReplyDelete
  4. ቀሲስ...ይቀጥላል…..ካሉኮ 10 ቀን አለፈው:: ሁለተናውን ክፍል አየጠበቅን ነው...

    ReplyDelete
  5. ቃለ-ህወትን ያሰማልን

    ReplyDelete