Tuesday 10 September 2013

5ቱ ስጦታዎች (ክፍል 2)

4.በኩራት
በኩር ማለተ የመጀመሪያ ማለት ሲሆን የበኩራት ስጦታ ከልጅ፤ከከብት፤ከንብረት… ከመሳሰለው የመጀመሪያውን መስጠት ነው፡፡የአዳም ልጅ አቤል መስዋዕት ሲያቅርብ ‹‹ የመጀመሪያውን ለየ›› የሚለው በኩራቱን ስለማቅረቡ ሲያስረዳ ሲሆን፡ ይህም የተወደደ መሥዋዕት ሆኖለታል /ዘፍ 4፤4/ ፡፡ከዘመነ ኦሪት ጀምሮ ሕዝበ እግዚአብሔር  አምልኮታቸውን ከሚገልጹበት አንዱ በኩራት ነበር፡፡ከልጆቻቸው፤ከምርታቸው.... በኩር  የሆነውን ለእግዚአብሔር ቤት ይሰጣል፡፡ /ዘኁ 3፤42፤ 1ሳሙ 2፤ ዘኁ 18፤15-17/፡፡
በኩራትን ማቅረብ እጅግ የተወደደ እና ከሁሉ የሚበልጥ የስጦታ ዓይነት ነው /ዘዳ.23÷19፤ ዘዳ.26/፡፡ክርስቲያኖችም ሁላችንም ሥርዓተ አምልኮ የምንገልጥበት አንዱ የሆነውን በኩራቱን በማቅረብ ሕገ አምላክን ልንጠብቅ ይገባል፡፡ይህንንም ከመጀመሪያ ምርታችን፡ ከመጀመሪያ ደሞዛችን ለእግዚአብሔር ቤት በመስጠት የተናገረውን ከማያስቀረው አምላካችን በረከት እንደምናገኝ በማመን ልንፈጽም ይገባናል /ዘዳ28÷1-15/፡፡
5.ዐሥራት
ዐሥራት አንድ አሥረኛ ማለት ነው፡፡ከሚያገኙት ገቢ አንድ አሥረኛውን ለእግዚአብሔር ቤት መስጠትን ያመለክታል፡፡ከሙሴ በፊት በዘመነ አበው የተጀመረ የእግዚአብሔር ሕግ ነው፡፡መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዐሥራት በስፋት ይገልጻል፡፡ከነዚህም ለአብነት ያህል በጥቂቱ እንመልከት፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዐሥራት አበ ብዙሓን አብርሃም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ወደ መልከ ጼዴቅ በሄደ ጊዜ ዐሥራት ማውጣቱን ‹‹አብርሃምም ከሁሉ ዐሥራት ሰጠው›› በማለት ዐሥራትን አበው እነደጀመሩት ያስረዳናል/ዘፍ 14÷20/፡፡ ያዕቆብ ከአባቶቹ የወረሰውን ሕገ አምላክ የሆነውን ዐሥራት ማውጣትን ሲገልጽ ‹‹ከሰጠኸኝ ሁሉ ለአንተ ከዐሥር አንዱን እሰጣለሁ›› ብሏል /ዘፍ 28÷ 1-22/፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዐሥራት ሲያስረዳን ከእግዚአብሔር የታዘዘ መሆኑን አጽንኦት በመስጠት  ነው፡፡ ‹‹ከምታገኘው ሁሉ ዐሥራትን ታወጣለህ›› የሚለው ‹‹ዐሥራት አስገቡ›› ማለቱ እነደዚሁም የምድር ዐሥራት የእግዚአብሔር መሆኑን የሚገልጹ ማስረጃዎች ሁሉ ዐሥራት ሕገ አምላክ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ /ዘዳ. 14÷22፤ ዘሌ.27÷30፤ ዘዳ.12÷17፤ ዘዳ.14÷23፤ ሚል.3÷10/፡፡
መድሓኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በመዋዕለ ስብከቱ ‹‹የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ስጡ›› ማለቱ አምላካዊ ትዕዛዝ መሆኑን ያስገነዝበናል /ማቴ 22÷17/፡፡እንደዚሁም አንድ ቀራጭ ወደ ጌታችን ቀርቦ ‹‹ከማገገኘው ዐሥራት አመጣለሁ›› ማለቱ ቀድሞ የነበረ ሕግ መሆኑን የሚያመለክት ሲሆን ጌታችንም ቀራጩን በዐሥራት ጉዳይ ላይ መልስ አለመስጠቱ ዐሥራት ተገቢ የሆነ ሥርዓት መሆኑን የሚያመለክት ነው /ሉቃ 18÷12/፡፡

ዐሥራት በመስጠታችን የምናገኘው ጥቅም ምንድን ነው?

ሀ. በረከት ይበዛልናል
ዐሥራት ማውጣት ትዕዛዝን መፈጸም ነውና በአምላካዊ ቃሉ መሠረት በረከቱን ያበዛልናል፡፡‹‹ ቃሌን ብትሰማ በረከቶች ሁሉ ላንተ ይሆናሉ›› በማለት ቃል እንደገባልን ዐሥራት በማውጣት ለቃሉ ብንገዛ ሀገር፤በት፤ትዳር፤ልጆች   ወዘተ ሁሉም እንደሚባረኩ የታመነ ነው /ዘዳ 28÷1-20/፡፡በነብዩ በሚልክያስ የተጻፈው ቃለ እግዚአብሔር እንደሚያረጋግጥልን የእግዚአብሔር ገንዘብ የሆነውን ዐሥራት በማውጣት ብንታዘዝ ‹‹የሰማይ መስኮትን እከፍታለሁ በረከትን እሰጣለሁ›› በማለት አስገንዝቦናል /ሚል 3÷10/፡፡
ለ. ለጽድቅ ያበቃል
‹‹ሕግን የሚሰሩ ይጸድቃሉ››  እንዳለ ዐሥራት ሕግን መፈጸም ነውና ለጽድቅ የሚያበቃ መሆኑን ልናምን ይገባል /ሮሜ12፤12/፡፡ሕገ እግዚአብሔርን  በመፈጸም ምሕረተ ሥጋ ወነፍስ የምናገኝ መሆኑንም በማይሻር ቃሉ እንዲህ ብሏል ‹‹ትዕዛዜን ለሚጠብቁ ምሕረትን የማደርግ እኔ ነኝ›› /ዘዳ 20÷6/፡፡ቅዱሳን ሐዋርያትም ከልብ በሆነ ፈቃደኝነት ዐሥራት በመስጠት ክርስትናችንን እንድንገልጽና ለጽድቅ  እንድንበቃ መክረውናል፡፡በመሆኑም ከምናገኘው ገቢ ላይ ከዐሥር አንድ አስበን ለእግዚአብሔር ቤት በመስጠት ለመንፈሳዊ ዋጋ ልንተጋ ይገባል፡፡‹‹በበረከት የሚዘራ በበረከት ያጭዳል›› ተብሏልና /1ቆሮ16÷14፤ 2ቆሮ 9÷6-12/፡፡
ነገር ግን በተቃራኒው ዐሥራት በስስትና በተለያዩ ምክንያቶች አለመክፈል ከእግዚአብሔር ጸጋ ያርቃል፡ መርገምንም ያመጣል፡፡‹‹ሰርቃችሁኛል…..ይኽም ዐሥራትና በኩራቴን ነው›› የሚለው ሃይለ ቃል የሚያስረዳውም ዐሥራት አለመክፈል ከእግዚአብሔር ገንዘብ ላይ መስረቅ መሆኑን ነው፡፡በነብዩ በኢሳያስ የተነገረውም ያለመታዘዝን ጉዳት ያስረዳል ‹‹እምቢ ብትሉ ሰይፍ ይበላችኋል›› /ኢሳ.1÷19/ እንዲል፡፡
ዐሥራት አከፋፈል
ዐሥራት መክፈል አምልኮተ እግዚአብሔርን ከምንገልጽበት ተግባር አንዱ መሆኑን ከተገነዘብን፡ አከፋፈሉንም በማስተዋል ልንፈጽም  ያስፈልጋል፡፡ዐሥራት ከገቢ /ከደመወዝ/ ከዐሥር አንዱን በየወሩ ለቤተክርስቲያን በመምህር ንስሐ በኩል ወይም በቀጥታ በመሔድ በየወሩ ልንከፍል ይገባል፡፡ የምንከፍለውን ዐሥራት ለገጠርም ሆነ ለአጥቢያችን ስናበረክት ማረጋገጫ መቀበልም ሳንዘነጋ ነው፡፡
አገልግሎቱም፡-
ሀ.ሥርዓተ አምልኮ ለማስፈጸም
የምንከፍለው አሥራት ለሥርዓተ አምልኮ ማስፈጸሚያ ይሆናል፡፡ከዘመነ ኦሪት ጀምሮ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስረዳን የቤተ መቅደስ መገልገያ እና አገልግሎቱ በዓሥራት ስጦታ ይሟላል/ዘዳ 27÷1/፡፡ስለሆነም ለሥርዓተ ቅዳሴ የሚያስፈልጉ፡ እና ለመንፈሳዊ አገልግሎት የሚውሉ ነገሮችን ሁሉ በካህናት አስፈጻሚነት ይሟላበታል፡፡
ለ.አገልጋዮችን ለመርዳት
በዘመነ ኦሪት ሌዋውያን በዐሥራት እንዲጠቀሙና በአግባቡ እንዲያገለግሉ ፈቃደ እግዚአብሔር በመሆኑ ለአገልጋዮች ይውላል /ዘኁ18÷21/፡፡በዚህም መሠረት በዘመነ አዲስም በፍትሐ ነገሥት እና በቃለ ዐዋዲ በተመዘገበው መሠረት የቤተክርስቲያን መደበኛ አገልጋዮች የሆኑ ካህናት ከሚገባው ዐሥራት ላይ ወርኃዊ ደመወዝ እያገኙ አገልግሎታቸውን እንዲፈጽሙበት ይውላል፡፡ ዐሥራትን ሳናስቀር በአግባቡ ብንከፍል እና አገልጋዮችም አግባብ ባለው ቦታ ላይ ቢያውሉት ዛሬ የምናየውን የአገልጋዮች መጉላላት፡ የአብነት ትምህርት ቤቶች መፈታት፡ በገጠር የካህናት እጥረት…. የመሳሰሉት ችግሮችን የሚቀርፍ ዋና አማራጭ መፍትሔ መሆኑ ሊስተዋል ይገባል፡፡
ሐ. ነዳያንና ጧሪ ቀባሪ የሌላቸው ይረዱበታል
ነዳያን ከሙዳየ ምጽዋት ብቻ እንደሚረዱ የሚስተምሩ መምህራን ያሉ ቢሆንም ከሕገ ቤተክርስቲያን ክፍል አንድ በሆነው በቃለ ዐዋዲ ላይ እንደተጻፈው በቤተክርስቲያን ዙሪያ የሚገኙ ደካሞች እና በተለያዩ ምክንያቶች መሥራት የማይችሉ ነዳያን ከምእመናን ከሚመጣው ዐሥራት ላይ ተቀንሶ በበጎ አድራጎት ክፍል አስተባባሪነት እንዲረዱበት ያዛል፡፡ በሙሴ እና ሌዋውያንም በስፋት በቤተመቅደስ በሚያገለግሉበት ዘመን ከዐሥራት ላይ ለነዳያን እንዲሰጡ እግዚአብሔር ስለማዘዙ ተጽፏል፡፡ስለዚህም ዐሥራት ለነዳያን የሚውል መሆኑንም ያረጋግጣል /ዘዳ.14÷28፡ 26÷12/፡፡
ማጠቃለያ
መንፈሳዊ ሕይወትን ለመምራት መንፈሳዊ ዕውቀትም ያስፈልገናል፡፡ስለሆነም የመንፈሳዊ ህይወት መገለጫ እና በረከት ማግኛ የሆኑትን ስጦታዎችን ለማበርከት ዓይነቶቹን እና ሥርዓቱን ለይተን ማወቅ ይጠበቅብናል፡፡‹‹ ቃሉን የምትፈጽሙ ሁኑ›› እንደሚል ማወቅ ደግሞ ለመፈጸም ነውና ስጦታዎቹን በረከት ለሕገ እግዚአብሔር በመገዛት ወደተግባር ልንገባ ያስፈልጋል፡፡ከእግዚአብሔር የተቀበልነውን ያለስስት፡ እና ያለ ጥርጥር ከልብ ሆነን ለእግዚአብሔር ቤት ልንሰጥ ይገባል፡፡‹‹በረከት እንደማልሰጥ ፈትኑኝ ›› ያለን አምላካችን በአግባቡ ለምንሰጥ በረከቱን ይሰጠን ዘንድ የታመነ አምላክ ነው /ሚል 3÷9፡ 1ቆሮ 9÷6/፡፡


(ውድ አንባቢያን ይህ ጽሁፍ በሐመር መጽሔት የየካቲት 2002 ዓ.ም. ዕትም ላይ ወጥቶ የነበረ መሆኑን እንገልጻለን !)ኸኸለኀኀኸኀኀኃደፈሸኸኀኀሃሐሃፈደፈደፈደ
 ኸኸለኀኀኸኀኀኃደፈሸኸኀኀሃሐሃፈደፈደፈደ

3 comments:

  1. ቃለ ህይወት ያሰማልን!!!



    ReplyDelete
  2. ቃለ ህይወት ያሰማልን!!!

    ReplyDelete
  3. Wynn Las Vegas Casino - Review - SEGA
    As a Las 온카지노 Vegas Strip หาเงินออนไลน์ casino, we can recommend Encore Las Vegas for the best septcasino gaming experience on the Strip, including slot machines, table games, and unique

    ReplyDelete