Wednesday 11 December 2013

ምኒልክ ማነው ?


ምኒልክ ማነው ? ”


(የአንድ ተቋም ሰልጣኞች ጥያቄ)

በአዲስ አበባ ፒያሳ አካባቢ የጋዜጠኝነት ስልጠና የሚሰጥ ተቋም አለ፡፡ አሰልጣኙ ስለ ቃለ መጠይቅ (ቃለ ምልልስ) እያስተማሩ የተለያዩ ምሳሌዎች እያቀረቡ ያስረዳሉ፡፡ በመካከል ‹‹ ለመሆኑ አፄ ምኒልክ የት ተወለዱ? ›› ብለው ጠየቁ ለተግባር ልምምድ መድረክ ላይ ለነበሩት ሰልጣኞች ቡድን ውስጥ መልስ የሚሰጥ አልተገኘም፤ ከ35 በላይ ለሆኑኑት በክፍሉ ውስጥ ለሚገኙት ጥያቄውን ደገሙት ወዲያው ‹‹ የቤት ስራ ይሁን›› ብለው ወጡ፡፡ ከ3 ቀናት በኃላ ገና እንደገቡ ሁለት ሰልጣኞች እጅ አወጡ ‹‹ ሳይቀድሙን…….. ›› ብለው ያሰቡ ይመስላል፡፡ ለአንዱ ዕድል ሰጡ ‹‹ ለመሆኑ ምኒልክ ማነው ? ›› ብሎ የቤት ስራ የነበረው ለመምህሩ የክፍል ስራ አድርጎ ጠየቀ ፡፡ መምህሩም እየተገረሙ ወደ አንደኛው እጅ አውጥቶ ወደነበረው    ‹‹አንተስ መልስ ነው ? ›› አሉት፡፡ ‹‹ አይደለም የእኔም ጥያቄ ይሄው ነበር ›› አለና አረፈው፡፡
#መጠየቅ ያደርጋል ሊቅ; ይባላል በጎ ነው፡፡ ግን ስለ አፄ ምኒልክ ጽሑፍ@ ነጋሪ@ ….. ጠፍቶ ይሆን? እውነት ግን የአሁን ዘመን ወገኖች አብዛኞቻችን ስለ ቀደምት የኢትዮጵያ ባለውለታዎች እናውቅ ይሆን? ታዲያ ለልጆቻችንስ ማን አስረዳቸው ?ለማንኛውም ከተረዳሁት ጥቂቱን ልመስክር ፡፡


ትውልድ
ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ስለ ተወለዱበት ብዙ ቢባልም በርካታ ጻሕፍት የመሰከሩት ሰሜን ሸዋ ደብረ ብርሃን እና አንጎለላ መካከል በባሶናወረና ወረዳ ዕንቁላል ኮሶ በምትባል ገጠርማ ቦታ ከሸዋው ንጉስ ኃይለመለኮት እና ከወ/ሮ እጅጋየሁ ለማ ነሐሴ 12/1836 ዓ.ም የዛሬ 170 ዓመት እንደተወለዱ ይነገራል፡፡ ከጥቅምት 25 ቀን/1882 ዓ.ም እስከ ታህሳስ 3 ቀን 1906 ዓ.ም ነገሱ፡፡ በዚህ ጽሑፍ አስተዳደግ እና ሹመትን ለአንባቢያን በመተው በይበልጥ ልንማርባቸው ስለሚገባን አስተዋጽኦ ጥቂቱን ልጠቁም፡፡

1-      የትምህርት መስፋፋት፡- ዘመናዊ ትምህርት እና ስልጣኔ በሀገራችን እንዲሰፋ አፄ ምኒልክ ስላደጉት አስተዋጽኦ የውጪ ምሑራን ጭምር ያረጋገጡት ሀቅ ነው፡፡ አሁን ድረስ የሚገኙ በስማቸው የታነፁ ተቋማት ሕያው ሐውልት ናቸው፡፡ ሥርዓተ ትምህርቱ ከቤተክርስቲያን ትምህርት ጋር እንዳይጋጭ ጥንቃቄ በማድረግ በዘመኑ የነበሩትን ሊቀጳጳስ አቡነ ማቴዎስን አነጋግረው ለግብጽ ጳጳስ ለአቡነ ቄርሎስ 5ኛ በ1898 ዓ.ም በደብዳቤ ‹‹ የሃይማኖት ትምህርታችን እንዳይፋለስ ክርስቲያን የሆኑ የዘመናዊ አስተማሪዎችን ላኩልኝ ›› ብለው በመላክ 3 መምህራን መጥተው በስማቸው የታነጸው ት/ቤት ከመፈጸሙ በፊት ከቤተመንግስታቸው በስተምዕራብ የፈረንሳዩ ልዑክ የላጋርድ መኖሪያ በነበረው ቤት ውስጥ ዘመናዊ ትምህር እንዲጀመር ሆኗል፡፡ ሕዝቡም በትምህት እንዲታነጽ እና እንዲቀበለው ልጆቹን ለማስተማር የማይልክ ሲሞት ንብረቱን መንግስት ይወርሰዋል ብለው ዐዋጅ እስከማስነገር በመድረስ ጥረታቸው እጅግ ጉልህ ነበር፡፡
(የዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ መጽሔት 1992 ዓ.ም  ዝክረ ነገር 1989 ዓ.ም)
2-      የግዛት ማስከበር፡- ኢትዮጵያ ግዛቴ ነው ብላ በዓለም አቀፍ ደረጃ ልትመሰክር የምትችልበትን የድንበር ማስከበር ላይ ንጉሱ ከፍተኛ ሚና የነበራቸው ወደ ጎረቤት ሀገር ሊካተቱ የነበሩ የኢትዮጵያ የሆኑ ግዛቶችን ዳር ድንበር ለይተው ማኖራቸው በይበልጥም ሶስት አዋሳኝቦታዎች የድንበር ማካለያ ማድረጋቸው አስተዋይነት እና ብሔራዊ አብነትነታቸውን የሚገልጽ ነው፡፡

3-      ፀረ ቅኝ ግዛት መሆናቸው፡- ከአፍሪካ ሀገራት በቅኝ ግዛት ‹‹ እሺ በጄ … ›› ብላ ኢትዮጵያ አልተገዛችም እያልን ለምንኮራበት ታሪክ ላበቁን አንድ ዳግማዊ ምኒልክ መሆናቸውን ከልጅነት ጀምረን ሲነገረን የኖረው ልዩ ታሪክ ነው፡፡ በብሔራዊ ደረጃ በሚከበረው የአድዋ ድል በግል የግዛትና የንግስና ሽኩቻዎች እንዲወገድ እና ማዕከላዊነት ያለው የአንድነት መንግስት እንዲመሰረት የደረጉት ተጋድሎ እና ውጤቱ ከበርካቶች መሪዎች ልዩ እና እውነትም ‹‹ ንጉሠ ነገሥት›› ያሰኛቸው ነው፡፡                           (የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1948 – 1966) ባሕሩ ዘውዴ)

4-      አብያተ ክርስቲያናትን ማስፋፋት፡- ስለ ዘመናዊ ትምህርት ባስነገሩት አዋጅ እና በተለያዩ ጊዜያት የሚናገሩት እንደሆነ የሚመሰክረው ‹‹ ትምህርት ከሌለ ቤተክርስቲያን አትኖርም ፤ ቤተክርስቲያን ከሌለች ክርስትና አይኖርም ›› ልዩ አባባላቸውን በስራ በመግለጽ በሀገራችን ከመንፈሳዊ በረከት ማግኛነቱ አልፎ ለሀገር ቅርስ እና ለቱሪዝም መስፋፋት አስተዋጽኦ እያደረጉ የሚገኙ በርካታ ገዳማትና አድባራትን በዘመነ መንግስታቸው ትኩረት ሰጥተው እግዚአብሔርን አክብረው አሳንፀዋል፡፡ ለአብነትም፡-
-           ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ
-           እንጦጦ ደብረ ኃይል ቅዱስ ራጌኤል
-           ደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል
-           መንበረ ፀባኦት ቅድስት ሥላሴ  . . .

እንኳንስ በሀገራችን በቅድስት ሀገር በኢየሩስአሌምም የኢትዮጵያ ይዞታዎች እንዲጠናከሩ እና የተለያዩ ገዳማትና ሕንጻዎች እንዲገነቡ አድርገዋል፡፡               (ቅድስት ሀገር በአማከለ ገበየሁ)
                                                  (የቤተክርስቲያን መረጃዎች ፤ በዲ/ን ዳንኤል ክብረት)

ንጉሠ ነገሥቱ ለሀገራችን ያዋሉት ውለታ በአጭር ጽሑፍ የሚገደብ እንዳልሆነ እሙን ነው፡፡ በእውነት ከሆነ በሁሉም መስክ ፋና ወጊ ነበሩ ዘመናዊ ወፍጮ፣ የስልክ አገልግሎት….. በማን ተጀመረና? አስከፊ ረሀብ ሀገራችን በዘመናቸው ሲከሰት በምዕመናኑ ጸሎት በእግዚአብሔር ቸርነት ከተወገደ በኃላ የበለጠ አዋጆቻቸው እና ሰርተው የሚያሳዩት ተግባር አሁን ላለነው መሰረት የጣለ መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡
ለምሳሌ፡- በጥቃቅንና አነስተኛ ለመደራጀት ፈር ቀዳጅ ነበሩ፡፡ አንጥረኞች፣ ባለእጆች……. እንዲደራጁ እውቅና እንዲሰጣቸው እና ሕዝቡም በስራ እንዲተጋ ባለሙያዎችንም እንዲያከብር በአዋጅ ያስከበሩ መሆናቸው ፤  የተፈጥሮ አደጋን ለመቋቋም እፅዋት እንዲተክሉ እንክብካቤም እንዲደረግ በስፋት ለመጀመሪያ ጊዜ ያዘዙ አፄ ምኒልክ አይደሉም እንዴ? ቀድሞ እና በዘመናቸው መጀመሪያ ላይ የተስፋፋው የባሪያ ንግድ ከመቃወም አልፈው እኩልነት እንዲሰፍን በአዋጅ እና በሕግ ማስከበራቸውን ታሪክ አይክደውም
                 (ብላቴን ጌታ ኅሩይ #ዋዜማ;@ ተክለፃድቅ መኩሪያ የኢትዮጵጣ ታሪክ)


ዜና እረፍት

ብዙዎች ምሑራን ከዛሬ 103 ዓመት በፊትበ1903 ዓ.ም ስመ ጥሩ ዳግማዊ ምኒልክ በጠና ታመው ዐረፉ ይላሉ፡፡ ዜና እረፍታቸው ሳይነገር ለሶስት ዓመታ ተደብቆ በ1906 ታህሳስ 3 በይፋ ተነግሮ በታዕካ ነገስት በዓታ ለማርያም ሥርዓተ ቀብር እንደተፈጸመላቸው ይመሰክራሉ፡፡ የመደበቁ ምክንያትም ‹‹ መኳንንቱ ወደ እርስ በእርስ ጦርነት ያመራሉ ፤ የሚወዳቸው ሕዝብ ይደነግጣል ፤ ሽፍትነት ይበረክታል……… ›› ተብሎ እና በተጨማሪም በጣይቱ ሰበብ በጎንደር እና በሸዋ ሰዎች መካከል የተፈጠረው ቅራኔ ፤ እንደዚሁም የልጅ ኢያሱ እና የራስ ቢትወደድ ተሰማ ቅራኔዎች እና መሰል ችግሮች እስከሚረግቡ የሞታቸው ዜና እንዲደበቅ ግድ ሆኗል፡፡ እንዲያውም ልጅ ኢያሱ ሐዘኑ እንዳይሰማ ካደረጉት ጥረት ውስጥ ሞቱ በተባለ ማግስት በጃንሜዳ ጉግሥ ሲጫወቱ መታየታቸው እና የሐዘን ልብስ አለመልበሳቸው ተጠቃሽ ታሪክ ነው፡፡

    ‹‹  ያስተማርኩህን በልብህ ያዝ ለልጅህም ንገረው ››  ዘዳ 6 * 7

እንደሚል ለሀገራችን አብነት ሆነው ለዛሬው ማንነታችን ተጠቃሽ የሆኑ አፄ ምኒልክ እና መሰሎቻቸውን በርካታ ምሑራን በጽሑፍ አውርሰውናል፡፡ በጎ ታሪክ መስራሰት የምንችለው፤ ታሪክ ስናውቅ ነው፡፡ በጎውን ታሪክ ያስረከቡ አበው የግድ የተፈጠርንባት ሀገር የማንነታችን መገለጫዎች መሆናቸውን መካድ የለብንም፡፡ አሜሪካዊ በሕንዳዊ ፤ ሕንዳዊ በአሜሪካዊ …… አይኮራም፡፡ እኛም በሌሎች ሳይሆን መጀመሪያ በራሳችን ባለታሪኮች እንኩራ፡፡ አሜሪካ በታሪኳ በእርስ በእርስ ግጭት ብዙ ሕዝብ ያለቀባት በአብርሐም ሊንከን ዘመን ነው፡፡ ግን ታሪክ ነውና እንኳንስ ባሸነፈው በተሸነፈውም በጀፈርሰን ታሪክ መኩራታቸውን ለመግለጽ በስሞቻቸው፣ ተቋማት፣ መንገድ፣ ……. ሰይመው ይዘክራሉ፡፡ እኛስ?

ለልጆቻችን ስለ ባለታሪኮቻችን እንዴት እንንገራቸው? በብሔር ብሔረሰቦች ቋንቋ ማን ጽፎ ይተርክላቸው? ዛሬ ‹‹ ምኒልክ ማነው? ›› ከተጠየቀ በቀጣዩ ትውልድ ‹‹ ምኒልክ የሚባል ነበር እንዴ? ›› ይባል ይሆን የታሪክ ተወቃሽ እንዳንሆን ታሪክን እንወቅ፤ እንመስክር፡፡
 
ቀሲስ ፋሲል ታደሰ
የታ/ነ/በዓታ ለማርያም የዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ
 መንፈሳዊ ት/ቤት የሐዲሳት ደቀመዝሙር

1 comment:

  1. መስፍን በትሩ5 November 2014 at 22:10

    እስኪ እንደዚህ ደግ ደጉን ንገሩን::

    ReplyDelete