Thursday 5 December 2013

leyu leyu ልዩ ልዩ


ኢትዮጵያ እና ሩሳሌም ግንኙነት
ሩሳሌም ነገረ እግዚአብሔር በብሉይ ሆነ በዘመነ ክርስትና በስፋት የተገለጠባት ቅድስት ሀገር መሆኗ ይታወቃል፡፡ ሀገራች ኢትዮጵያም ከኢየሩሳሌም ሆነ ከሌሎች ቀደምት ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት በስፋት የሚነግረን የመጀመሪያው ማስረጃ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በአምልኮተ እግዚአብሔር የኖረች በርካታ ድንቅ ነገር የተመሰከረላት ስለመሆኗ እና የመሳሰለውን መጽሐፍ ቅዱስ ከ 41 ጊዜ በላይ በመጥቀስ ገልጾታል፡፡ መዝ 67*31
ከክርስትና በፊት በብሎይ ኪዳን እምነትና ስርዓተ አምልኮ ከኢየሩሳሌም ቀጥሎ ሕገ ኦሪትን በመቀበል ሁለተኛዋ ሀገረ እግዚአብሔር የሆነችው ኢትዮጵያ ከተጓዳኝ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ጋር የነበራት ግንኙነት ምን ጊዜም ሲዘከር የሚኖር ታሪካዊ ነው፡፡ ግንኙነቱም ይደረግ የነበረው
+ የብሉይ ኪዳን እምነትና ሥርዓተ ትውፊት በመጋራት

+ በዓመት አንድ ጊዜ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ላይ በመገኘት  የፋሲካን   በዓል በህብረት በማክበር
+ አንድ ዓይነት ሕግ መጽሐፋዊ ተጠቃሚ በመሆን እና በመሳሰሉት ነው፡፡
ይህም ግንኙነት የሀገር ርቀት ሊገታው በማይችለው ሂደት ላይ የቱን ያህል ጸንቶ የኖረና የሚኖር መሆኑን ከታሪክ ብቻ ሳይሆን በአሁኑም ዘመን ጎልቶ ከሚታየው የባሕል ግንኙነት ለክብረ በዓል በርካታ ምዕመናን መጓዝና የዴር ሱልጣን ሁኔታ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያም የመጀመሪያዋ የውጭ ግንኙነት ያረገችው ከኢየሩሳሌመ ጋር መሆኑንም ያመለክተናል የንግስቲቱ ጉዞ ቀድሞም ሀገራቱ ግንኙነት እንደነበራቸው ማስረጃ ነው፡፡

 
1  የንግስተ ሳባ ጉብኝትና ውጤቱ ፡-
ከክርስቶስ ልደት በፊት ከአንድ ሺህ ዓመተ ዓለም አካባቢ ከተደረገው በንግስተ ሳባ የኢየሩሳሌም ጉብኝት በኋላ ኢትዮጵያ በመንፈሳዊም ሆነ በማኅበራዊ ዕድገት በኩል ያገኘችው በረከት በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡ ስለተገኘውም በረከት ለመጠቆም ያህል

* የብሉይ መፍሐፍት ባለቤት
* የታቦተ ሕግ መንበረ (ታቦተ ጽዮን መግባቷ) 
* የክህነት አገልግሎት መስፋፋት
* የስርዓተ ኦሪት አስፈጻሚ ሀገር ለመሆን መቻሏና ወዘተ

ከጉብኝቱ የተገኙ ውጤቶች ናቸው፡፡ 1ኛ ነገ 10*1-9,  ማቴ  12*42 በሕገ ልቡና አምልኮቷን ስትገልጥ የቆየችው ሀገራችን ከንግስተ ሳባ ጉብኝት በኋላ ሌዋውያን የብሉይ መጽሐፍት እና ታቦተ ጽዮንን ይዘው በመግባታቸው ኢትዮጵያ በሕገ መጽሐፋዊ ወደ መመራት ተሸጋግራለች፡፡

2 ኢትዮጵያና ኢየሩሳሌም በዘመነ ክርስትና

እስራኤላዊና የእስራኤልን እምነት የተቀበለ ወንድ ልጅ ሁሉ በዓመት ሶስት ጊዜ የሚያከብራቸው እጅግ የተከበሩ በዓላት ሶስት ናቸው፡፡ እነዚህም

- የቂጣ በዓል (በዓለ ናዕት)
- በዓለሰዊት
- በዓለመጸለት (የዳስ በዓል) ናቸው።

እነዚህ በዓላት እስራኤላዊ ወንድ ሁሉ እግዚአብሔር በመረጠው ቦታ ማክበር ግዴታው መሆኑን ኦሪት ያዛል፡፡ ዘዳ 16*16

ይህን ሐይማኖታዊ ሕግ መሠረት በማድረግ ሕገ ኦሪትን የቀበሉ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ እግዚአብሔር ወደ መረጠው ቦታ ወደ ኢየሩሳሌም እየሔዱ በዓል ያከብሩ ነበር።

በሕጉ መሠረት እስራኤላውያን ከፋሲካ በኋላ ሱባዔ ቆጥረው በዓለ ሰዊትን ሲያከብሩ ኢትዮጵያውያን ምዕመናን እየተገኙ በአንድነት እግዚአብሐርን ያመሰግኑ ነበር፡፡ (ሶፎንያስ 3*0)

በዘመነ ክርስትናም ልማድ ስለቀጠለ ከትንሳኤ በኋላ በ 34 ዓም ይህን በዓል ሲያከብሩ ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው በሀገሩ ሁሉ (በ72) ቋንቋዎች ሲናገሩ እና ሲያመሰግኑት ከሰሙት መካከል ኢትዮጵያዊያን እንደነበሩ አበው ይናገራሉ።


 ቅዱሳን ሐዋርያት ጸጋ መንፈስ ቅዱስ በተቀበሉበት ወቅት ከተገኙ የዓለም ምዕመናን መካከል ኢትዮጵያዊያን ነበሩ ሲል ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ጽፏል፡፡ (ድርሳን ዘቅ ዮሐ አፈ) ሐዋ 2*1-13

የኢትዮጵያውያን ንግስት ሕንደኬ ሙሉ ባለስልጣን የነበረው ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ ሕገ ኦሪት በሚያዘው መሠረት በ34 ዓም ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ በዓሉን አክብሮ ሲመለስ በጋዛ መንገድ ከወንጌላዊ ፊሊጶስ ጋር ተገናኘ ጃንደረባውም ትንቢተ ኢሳያስ ምዕራፍ 50 እያነበበ ነበርና ቅዱስ ፊሊጶስ ተርጉሞ አስተምሮት ለክርስትና ጥምቀት አብቅቶታል፡፡ ሐዋ 2*1-13

የቤተክርስቲያን የታሪክ አባት የተባለው አውሳቢዎስ ዘቂሳርያ ይህን ሲገልጽ ከእስራኤል ሕዝብ ቀጥሎ በክርስቶስ አምኖ በመጠመቅ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ የመጀመሪያ የወንጌል ፍሬ ነው፡፡ ብሏል፡፡ (አውሰንዮስ ዘቂሳርያ የቤ/ታሪክ 2ኛመጽሐፍ)

ከቅዱሳን ሐዋርያት መካከል ቅዱስ ማቴዎስ፣ ቅዱስ ናትናኤል፣ ቅዱስ በርተሎሜዎስ፣ ቅዱስ ቶማስ በኖብያና በኢትዮጵያ ስለመሰበካቸው የታሪክ ጸሐፊዎት እነ ሩጼኖስና ሶቅራጥስ መስክረዋል፡፡

በይበልጥ ቅዱስ ማቴዎስ በስፋት ማገልገሉ ይታወቃል፡፡ ይህን የመሳሰለውና ሌሎችም ማስረጃዎች የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ይገልጻሉ፡፡ 

ቀሲስ ፋሲል ታደሰ
የታ/ነ/በዓታ ለማርያም የዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ
 መንፈሳዊ ት/ቤት የሐዲሳት ደቀመዝሙር








 

 


No comments:

Post a Comment