Thursday 18 July 2013

ምክረ ካህን



“መፋታትን እጠላለሁ ”ሚል 2÷16

ጋብቻ እግዚአብሔር የፈቀደው ክቡር ነው በይበልጥም በስርዓተ ቤተክርስቲያን በንስሐ እና በቅዱስ ቁርባን የሚፈፀም ጋብቻ ቅዱስ ጋብቻ ነው፡፡ ኤፌ 5÷32 ማቴ 19÷5 ሆኖም ግን ጋብቻ የበዛውን ያህል ፍቺም እየበዛ መሆኑ ግልፅ ነው በርካቶችም ወደ ፍቺ የሚያመራ ትዳር ውስጥ እንደሚገኙ ይናገራል ስለሆነም በዚህ እትም በምክረ ካህን ዓምድ የፍቺ ምክንያቶችና ፍቺ እንዳይገጥም መፍትሔዎችን በጥቂቱ እናስነብባለን፡፡
እግዚአብሔር ፍቃዱ በጽናት እንድንኖር ነው እንጂ ፍቺን እንደሚጠላ “መፋታትን እጠላለሁ” የሚለው አምላካዊ ቃል ያስረዳናል፡፡ ከጋብቻ በፊት የመጠናናት ዓላማ ክፉ፣ደግ ጠባያቸውን ለይተው ተቻችለው ለመኖር መሰረት የሚጥሉበት ነው፡፡ ሆኖም ግን አንዳንዶች በአግባቡ ሳይጠናኑ ወይም ስለ ጋብቻ ኑሮ በቂ ግንዛቤ ሳይኖራቸው ወደ ትዳር ሲገቡ ከመኖር ይልቅ ፍቺ ሲገጥማቸው ይታያል በርግጥ በዝሙትና በሀይማኖት ልዩነት ፍቺ ሊኖር እንደሚችል ይታወቃል ከተስተካከሉ ወይም ችግራቸውን ካስወገዱና ከተስማሙ ከፍቺው ይልቅ አብሮ መኖር የተመረጠ ነው፡፡ ሉቃ 16÷18   ማቴ 19÷9
በዘመናችን በርካቶችን ለፍቺ የዳረጉ ነገሮች ምን ይሆኑ?


1. ዝሙት፡- ጠቢቡ ሰሎሞን “ከሚስት ጋር ብቻ ደስ ይበልህ” በማለት ባለትዳሮች እንዲወሰኑ ሲመክር የአምላካችን ህግም አታመንዝር ይላል፡፡ ምሳሌ 18÷1 ዘጸ 20÷1 ነገር ግን ለትዳር ባለመታመን ወደ ሌላ ለመሄድ ለፍቺ የተጋለጡ እጅግ እየበዙ ይገኛሉ፡፡ በማመንዘር የተገኘ ወይም የተገኘች ራሱን የጠበቀ ይቅርታ አድርጎ ካልተስማሙ በቀር የዝሙት ጉዳይ ማፋታቱ ህጋዊነት አለው፡፡ “ያለዝሙት ምክንያት” ይላልና ማቴ 19÷7-9 ዝሙት ከእግዚአብሔር ጸጋ የሚያርቅና ከጥሩ ቤተሰብ አንድነት የሚለይ የነውር ተግባር ነው፡፡
2. የአስተሳሰብ ልዩነት እና አለመግባባት፡- አንዳንዶች በአስተሳሰብ አልተግባባንም በሚል ከንቱ ምክንያት ለፍቺ ሲደርሱ ይታያሉ፡፡ በደንብ ሳይተዋወቁ የተጋቡ በይበልጥ ይህ ይከሰትባቸዋል፡፡ በግልጽ መነጋር ሲገባቸው በካህንና በሽማግሌ ችግሮቻቸውን መፍታት ሲችሉ ገና ለገና መቼም አንግባባም በሚል የስህተት አስተሳሰብ የተቀደሰውን ጋብቻ በፍቺ ሲያረክሱ ይስተዋላል ስለዚህ የአመለካከት ልዩነት ለማጥበብ ከመምከር ይልቅ ባለመግባባት የሚፈጠር ፍቺ እየበዛ ሔዷል፡፡
3. በሩካቤ አለመጣጣም፡- ከጋብቻ ዓላማ አንዱ ከዝሙት ጠንቅ ለመዳን መሆኑ ይታወቃል፡፡ 1ኛቆሮ 7÷1-7 አንዳንድ ባለትዳሮች ስለሩካቤ ግልጽነት በመነጋገር አዕምሮአቸውን አሳምነው መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ በልባቸው ችግራቸውን ይዘው ይቆያሉ በሂደት ባለመጣጣም ምክንያት እርካታ ማጣት ሲያይልባቸው በግልጽ ሳይናገሩ የተለያዩ ሰበቦችን በመደርደር ለፍቺ ይወስናሉ ይህ ችግር ተመካክረው ቢሆን የስነ ልቦና ዝግጅት በማድረግ የሚፈቱት ይሆን ነበር፡፡ በርግጥ ይህ ችግር ከባድ ቢመስልም ነገር ግን መፍትሔው ደግሞ በሁለቱ እጅ በመነጋገር የሚገኝ በመሆኑ በጣም ቀላል ነው፡፡ ትዳርን ያህል ነገር ከማበላሸት ልጆችን ከመበተን በፊት ግልጽነት በተሞላበት መልኩ ተነጋግረውና ካህንን እና የስነ ልቦና ባለሙያዎችን አማክረው ለመፍትሔ ቢዘጋጁ መልካም ነው፡፡ በይበልጥም ቀሳውስት እንደዚህ አይነቱን ችግር በመረዳትና በቂ ምክር በመስጠት ከፍቺ የመጠበቅ አደራ አለብን፡፡ “በትዳር ጉዳይ ይቅርና በመላዕክት እንኳን እንድንፈርድ አታውቁምን” 1ኛቆሮ 6÷3 እንደሚል
4. ጣልቃ ገብነት፡- ለፍቺ እየዳረጉ ከሚገኙ ምክንያቶች ውስጥ የሶስተኛ ወገኖች ጣልቃ ገብነት ነው፡፡ በተዋደዱ ሰዎች መካከል ገብተው ጸብን የሚዘሩ የክፉ ወሬ መልዕክተኞች ተበራክተዋል፡፡ ጓደኞች፣ቤተሰቦች ሊሆኑ ይችላሉ ነገር ግን ከክፉ ቅናት ወይም ደግ መካሪ መስለው ባለትዳሮች ለፍቺ የሚያዳርስ ወሬ በማውራት የለያዩትን ቤቱ ይቁጠረው በዘር በመለያየት ባለመውለዳቸው እና በመሳሰሉት ምክንያት እየደረደሩ ወሬ የሚዘሩት እና ባለትዳሮችም ከመነጋገር ይልቅ ለክፉ ወሬ ቦታ በመስጠት እና በማመን ወደ ፍቺ ሲያመሩ እየታየ ነው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ “በማስተዋል ኑሩ ” እንደሚል ባለትዳሮችም ሊያስውሉና ወሬኞችም ሊታረሙ ይገባል 1ኛ ጴጥ 3÷7
ፍቺ እንዳይከሰት ምን ይጠበቅብናል፡-
1. ግልጽ መሆን፡-
እንኳንስ በትዳር ላይ ከቅድመ ጋብቻ ጀምሮ ግልጽነት በጣም ወሳኝ ነው፡፡ የትዳር አጋራችንን እንዴት እንፈራለን? ምንስ እንደብቃለን? ቅዱስ መጽሐፍ አንድ ስጋ ይሆናሉ በማለት አንድነታቸውን የገለጠላቸው ባለትዳሮች ውስጣዊ ስሜታቸውን ደስታና ችግራቸውን በግልጽ መነጋገር ከቻሉ ለፍቺ አይዳረጉም ፍቅራቸውም ዘላቂ ይሆናል ኤፌ 5÷32 ማቴ 19÷1 በስሜት መጣጣም የሚገኘው እና እውነተኛ ፍቅር የሚዳብረው በግልጽ ሲነጋገሩ ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም መደባበቅ ለውሸትና ለፍቺ እንደሚዳርግ በማመን ግልጽነት መለማመድ ግድ ይላል፡፡
2. ጥፋተኝነትን ማመን፡- ብዙ ጊዜ የተለያዩ ስህተቶች ሲፈጠሩ ጥፋተኛው አምኖ ይቅርታ መጠየቅ ሲገባው ባለማመን ላለመሸነፍ በሚደረግ ሙግት የበርካቶች ትዳር ፈርሷል ስህተትን ማመንና ይቅርታ መጠየቅ ለትዳር ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ዋጋ የሚያስገኝ የክርስቲያናዊ ህይወት ነው ሁል ጊዜ ላለመሳሳት ከተሳሳትንም ጥፋታችንን አምነን ለመታረም ፈቃደኛ እንሁን ጥፋትን ማመን ክብርን የሚነሳ አይደለም፡፡
3. ከክፉ ወሬ መሸሽ፡- ከላይ እንደገለጽነው ክፉ ወሬ ሰምተን ወደ ፍቺ ከመሄድ ይልቅ ወሬውን አለመስማት ቦታ አለመስጠት እና ለትዳር ትኩረት መስጠት ይጠበቅብናል፡፡ ክፉ ወሬ እስራኤል ከነአን እንዳይገቡ መሰናክል እንደሆነባቸው ዛሬም በትዳር በኩል የሚገኘውን በረከት ወሬ እንዳያሳጣን ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡ ዘጸ13÷25 በመጀመሪያ ደረጃ ባልና ሚስት የሚደባበቁት ሚስጥር ሊኖራቸው አይገባም ይህም ፍቅራቸውን ከማጠናከሩ በተጨማሪ ለጠላት ወሬም በሩ እንዲዘጋበት ያደረጋል፡፡ ወሬ ሲሰሙም በእርጋታ በመነጋገር መፍትሔ ላይ መድረስ እንጂ በወሬ ምክንያት ሊወነጃጀሉ አይገባም፡፡
4. በምክረ ካህን መመራት፡- ባለትዳሮች በንስሐ እና በመንፈሳዊ ምክክር ከንስሐ አባታቸው ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ቀሳውስትን ቤታቸው ጠርተው መጋበዝና የማይመለከታቸውን ወሬ ማውራት ሳይሆን በትዳራቸው ዙሪያ በጥልቀት መመካከር ይጠበቅባቸዋል፡፡ በምክረ ካህን ከተመራን ከንስሐ ምግባራትና ከቅዱስ ቁርባን ሳንለይ ለመኖርና ከፍቺ የራቀ እውነተኛ ክርስቲያናዊ ጋብቻ ለመምራት ያስችለናልና ነው፡፡ በአጠቃላይ ባልና ሚስት በማንኛውም እንቅስቃሴያቸው ውስጥ ለፍቺ ምክንያት ከሚሆኑ ነገሮች ውስጥ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል ቸግሮች ሲከሰቱ ከምን እንደመጡና ለመፍትሔ መዘጋጀት እንጂ ለፍቺ ውሳኔ መቸኮል አይገባቸውም ምክንያቱም ፍቺ እግዚአብሔር የሚጠላው ሀጢአት ከመሆኑም ባሻገር ለቤተሰብ መበተን ለስነ ልቦና ችግር ለኑሮ መዛባት እና ለበርካታ ችግሮች የሚዳርግ ነውና “መንፈሳችሁን ጠብቁ ማንም የልጅነት ሚስቱን አያታልል መፋታትን እጠላለሁ” ይላል የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሚል2÷16


5 comments: