Friday 12 July 2013

ነገር በምሳሌ….



በግ በውሻ ቀና
ሊቁ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ስኳርና ወተትየሚል ከእንግሊዘኛ የተተረጎመ በ1922ዓ.ም ከፃፉት ተረት መጽሐፍ ላይ የጠቀሱትን እንመልከትና እንማርበት፡፡ ምሳሌ ማስተማሪያ መንገድ ነው፡፡
ብዙ በጎች ያሉት አንድ ሰው ነበር እርሱም በጎቹን ሲጠብቅ በብዙ ጥንቃቄ ነው፡፡ የለመለመ ሳር ይመግበቸዋል፣ የጠራ ውሃ ያጠጣቸዋል ሲመሽም ወደ ጉሮኗቸው ያስገባቸዋል፡፡ በዚህ መልኩ በጣም ይንከባከባቸዋል፡፡ ከአንዱ ግልገል በቀር ሁሉም ጠባቂያቸውን ይወዳሉ፡፡ ያ አንዱ ግልገል ግን ጠባቂውን አይወድም፡፡ አንድ ቀን ወደ እናቱ ቀርቦ እናቴ ሆይ እኛ ማታ ማታ ለምን ይዘጋብናል እነሆ ውሾች ሳይዘጋባቸው እየተጫወቱ ያድራሉ፡፡ እኔም ከአሁን በኃላ እንደ ውሾች ማታ ማታ መጫወት እፈልጋለሁኝአላት፡፡ እናቲቱም ልጄ ሆይ አርፈህ ተቀመጥ ጠባቂያችን እጅግ መልካም ነው እርሱ እንዳዘዘን ውለን ብንገባ ይሻለናል፡፡ እንቢ ያልክ እንደሆነ በራስህ ላይ ጥፋት ታመጣለህ አለችው፡፡ 

 
ግልገሉም ይህን በሰማ ጊዜ እናቴ ሆይ መልካም ምክር አልመከርሽኝም እኔስ እንደ ውሾቹ መሆኔን አልተውም አለ፡፡ ከዚህ በኃላ ጠባቂያቸው እንተለመደው ሲመሽ ሲያስገባቸው ያ ግልገል ተደብቆ ቀረ ጠባቂው ሁሉም የገቡ መስሎት ቤቱ ገባ፡፡ ጊዜው ሲጨልም በውሾች የቀናው ግልገል ከተደበቀበት ወጥቶ ከውሾች ጋር መሯሯጥ ጀመረ፡፡ ከጉረኖውም እየራቀ ሄደ በድንገትም አንድ የተራበ ተኩላ አይቶት አባረረው ውሾቹም ተበታተኑ በጉም ርቋልና ወደ ጉረኖው መድረስ ተቸገረ ተኩላውም ደርሶበት አቅፎ ወስዶ ወደ ጉድጓድ አግብቶ ገነጣጠለው፡፡
ምከረው ምከረው እምቢ ካለ መከራ ይምከረው እንዲሉ በጎ ምክር የማንሰማ ከከበረ ኑሮ ይልቅ የጨለማውን ለእኛ የማይገባ የኃጢአት ኑሮ የምንመርጥ እየበዛን ነው፡፡ ከመንፈሳዊ መዝሙር ይልቅ በዘፈኑ፣ ከቅዱሳን ይልቅ በሀጥአን የምንቀና እንደነሱ ካልሆንን የምንል እንደ በጉ ግልገል ሳይገጥመን በቤተክርስቲያን እንጽና፡፡ ሕዝቤ ሆይ ወደ ቤትህ ግባ ደጅህንም በኃላ ዝጋ አሳ 26÷20
ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን፡፡

1 comment: